የመንገድ ግንባታ ኘሮጀክቶችን ሥራ የሚያከናውኑ ተቋራጮች፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታ አጠናቀው እንዲያስረክቡ ከንቲባ ከድር ጁሀር አሳሰቡ።

የመንገድ ግንባታ ኘሮጀክቶችን ሥራ የሚያከናውኑ ተቋራጮች፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታ አጠናቀው እንዲያስረክቡ ከንቲባ ከድር ጁሀር አሳሰቡ። የድሬዳዋ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን፤የመንገድ ፕሮጀክቶች የሚገኙበትን ደረጃ ከግንባታ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች፣ ማህበራትና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተገምግሟል። በመድረኩ ላይ በባለስልጣኑ እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ ኘሮጀክት ግንባታዎች፤ የ9 ወራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ የአብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደተጓተተም በሪፖርቱ ተገልጿል። የግንባታዎቹ መጓተት በተለያዩ ምክንያቶች የተከሰተ ነው ያሉት ተቋራጮቹ በቀጣይ የማስተካከያ ስራዎች እንሰራለን ብለዋል። የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ወርቅነህ በበኩላቸው፤ የቀረቡት አብዛኞቹ ምክንያቶች ተገቢነት እንደሌላቸው፤ ተቋራጮቹ የፕሮጀክቶቹን ግንባታ በአግባቡ እንደማይከታተሉና፤ በውሉ መሠረት እየሰሩ እንዳልሆነ ገልፀው፤ ይህ አሰራር ተቀባይነት ስለሌለው መስሪያ ቤታቸው በህጉ መሠረት ለመጠየቅ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። “የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በተገቢው ፍጥነት ባለመጠናቀቃቸው የአስተዳደራችን ነዋሪዎች አገልግሎት እያገኙ አይደለም” ያሉት፤ በአስተዳደሩ ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ የሆኑት አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ፤ በቀጣይ በፕሮጀክት ቀረፃና ተቋራጭ መረጣ ላይ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን መንግስት እንደማይታገስና፤ የተጀመሩትን የመንገድ ግንባታዎች አጠናቅቀው በማያስረክቡ ተቋራጮችና ቁጥጥር በማያደርጉ የመንግስት አመራሮች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል። በግምገማ መድረኩ ማጠቃለያ ላይ፤ የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር፤ በህዝብ ጊዜ እና ንብረት ላይ የሚቀልዱ የግንባታ ተቋራጮችን፣ ተቆጣጣሪዎችንና ማህበራትን የምንታገስበት ምክንያትና ተጨማሪ ጊዜ የለንም ብለዋል። በገቡት ውል መሠረት የጥራት ደረጃውን ጠብቀው ግንባታ የማያጠናቅቁ ተቋራጮች፤ ወደፊት በምንም አይነት የአስተዳደሩ ግንባታዎች ላይ እንደማይሳተፉ ያስታወቁት ከንቲባ ከድር ጁሀር፤ የ2014 በጀት ዓመት ከማለቁ አስቀድሞ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቅቀው ለህዝብ አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። ድሬዳዋ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት

Loading

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *