ብልጽግና – ለዜጎች ክብር የሚሰራ ፓርቲ!

ዜጎቿን ያላከበረች አገር በሌሎች ልትከበርና ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ ሊኖር አይችልም፤ ዜጎቿን በሁለንተናዊ መልኩ ማክበር የቻለች አገር ግን ለዜጎቿ በሰጠችው ክብር ልክ ከፍ ብላ ትታያለች፣ ሉዓላዊነቷም ተከብሮ ትኖራለች፡፡ አገር ዜጎቿን ትመስላለች የሚባለውም ለዚህ ነው፤ ዜጎችም የአገራቸው ገጽታዎች ናቸውና!!

ብልጽግና ፓርቲ በመደመር መስመር መዳረሻውን በሁለንተናዊ ብልጽግና ለማሳካት ጉዞ የጀመረው የዜጎችን ክብር በማስቀደም ነው፡፡ ብልጽግና የዜጎች ወይም ሰዎች ክብር በአገር፣ በቡድንና በግለሰብ ደረጃ የሚገለጽ መሆኑን በማመን እንዲሁም የአገር ክብር የግለሰቦች የወል ክብር መሆኑን በጥልቅ በመረዳት ኢትዮጵያዊያን የሚመኙትንና ሁልጊዜም እየፈለጉና እየሞከሩ በሚፈልጉት ልክ ያላገኙትን ሰው በመሆን የሚቀድም አብሮነት እውን ለማድረግ እየሰራ ያለ የህዝብ ፓርቲ ነው። ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ለረጅም ዓመታት እየፈተናቸው ያለውን ጉድለትና ጉድለቱን ሞልቶ ወደ ብልፅግና ለማሸጋገርም ቀዳሚው ጉዳይ የዜጎች ክብርን ማረጋገጥ በመሆኑ ለዜጎች ክብር የትኛውንም አይነት ዋጋ በመክፈል ብልፅግናን ለማረጋገጥ ቆርጦ ተነስቷል።

በብልጽግና እምነት ሰዎች ወይም ዜጎች ሁልጊዜም ወደ ግብ መቅረቢያ መንገድ ሳይሆኑ ራሳቸው ግብ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች አንድን ነገር ለማግኘት ወይም ለማሳካት ሲባል ብቻ የሚያስፈልጉ፣ አለያም ገሸሽ የሚደረጉ አይደሉምና፡፡ ይልቁንም ዜጎች በራሳቸው ከሁሉም ነገር ቀድመው የሚቀመጡ፤ የሚከበሩ፣ በማንነታቸውም ሳይሸማቀቁና ሳያፍሩ ቀና ብለው መሄድ የሚችሉ መሆናቸውን ማመን ይገባል፡፡  

ብልጽግና ስለ ዜጎች ክብር መናገር ብቻ ሳይሆን፤ የተናገረውንና ያመነበትን እየተገበረ ያለ ፓርቲ ነው፡፡ በዜጎች መከበር ውስጥ የአገር ክብርና ሉዓላዊነት እውን እንደሚሆንም በጥልቅ ያምናል፡፡ እምነቱን እውን ለማድረግም ገና ከጥንስሱ በለውጥ ማግስት ያከናወናቸው ዜጋ ተኮር ተግባራትና በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በአደባባይ የገለፁት እምነትና ያሳዩት ተስፋ ህያው ምስክር ነው፡፡

የፓርቲያችን ፕሬዚዳንት በጠቅላይ ሚኒስትርነት በዓለ ሲመታቸው ወቅት በህዝብ እንደራሴዎች ፊት ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር ቀዳሚ ያደረጉት  የዜጎችን ታላቅነትና ክብር መግለጽን ነበር፡፡ በዚህም ከአሁን በፊት ተደርጎ በማያውቅ መልኩ በኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን ለተፈጸመው በደል ሁሉ በአደባባይ ህዝብን ይቅርታ በመጠየቅ ለሰው ልጆች ሰብዓዊ ክብር ያላቸውን ጥልቅ መረዳት  ገለጹ፡፡ በዚህም ፓርቲም ሆነ አገር  ከዜጎችም በላይ ያለመሆኑ በተግባር ታየ፡፡ አገር ከምንም በላይ ለዜጎቿ ክብር ስትሰጥ እንደምትፀናና እንደምትበለፅግ በግልፅ ግንዛቤ እንዲያዝ ተደረገ፤ ኢትዮጵያውያንም በዚህ ጥልቅ መረዳት አንድ ዓመት ያህል በዘለቀው ፓርቲያችን ብልፅግናና በመሪያችን ላይ ያላቸውን ፅኑ እምነት ይዘው ተጉዘዋል። ፓርቲያችን ይህንኑ እውን ለማድረግ በሚያስችለው ምቹ የምርጫ አጋጣሚም ቃሉን በተግባር ለመቀየር ዝግጁነቱን አረጋግጧል።

ብልጽግና በይቅርታ ጉዞውን አንድ ብሎ ሲጀምር፤ ቀጣይ ስራዎቹን በወጉ ተረድቶ ለመከወን እና ስለ ህዝብ የገባውን ቃል ለመፈጸም ህዝቤ ምን ይላል በሚል በመላው ኢትዮጵያ በመዘዋወር ከህዝብ ጋር መክሯል፡፡ ችግሮችን፣ ፍላጎቶችን፣ አቅምና ክፍተቶችን የመለየት እድል አግኝቷል፡፡ ስለ ህዝብ ዝቅ ብሎ መጓዙና ህዝብን ከፍ እንዲል እድል መስጠቱ ላለፉት ሶስት ዓመታት ላከናወናቸው ተግባራት፣ ለወሰዳቸው እርምጃዎችና ማስተካከያዎች እንዲሁም ለቀጣይ ጉዞው ስንቅ የሚሆን የመማር እድል ትልቅ አቅምም መንገድም ሆኖታል፡፡

ባለፉት ሶስት ያክል ዓመታት  ያከናወናቸው የህዝብን ከፍታ የሚገልጹ ስራዎችም የዚህ ቀጣይ ክፍሎች ሲሆኑ፤ እነዚህም ብልጽግና ስለ ዜጎች በማንነት ያለማፈር እና ከአገር ውስጥ እስከ በውጭ አገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን እንደ ሰው ሊከበሩ፤ እንደ ዜጋ ሊታቀፉ እንደሚገባ ያሳየበትን አርኣያነት ያላቸው ተግባራት ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ከሰው ይልቅ ፖለቲካ፤ ከህዝብና አገር ይልቅ የቡድንና ግለሰቦች ጥቅም ሃያል ሆኖ የታያቸው አካላት በርካታ ዜጎችን ለእስር ዳርገው ነበር፡፡ ብልጽግና ከፖለቲካ ይልቅ ሰው፤ ከቡድንና ግለሰቦች ጥቅም ይልቅ የአገርና ህዝብ ልዕልና የላቀ መሆኑን በመገንዘብ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ከታሰሩበት እንዲፈቱ በማድረግ ለዜጎች ያለውን ተቆርቋሪነት አሳይቷል፡፡

በተለያየ መልኩ ከአገር ተሰድደው በውጭ አገራት የሚኖሩ ነገር ግን አገራቸው ብትናፍቃቸው፣ ወገን ዘመን ችግር ቢገጥመው መጥተው መጎብኘት የማይችሉ የነበሩ ወገኖች ወደ አገራቸው እንዲገቡም አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ በተለያዩ አገራት ሆነው ስርዓቱን በጦር እናስወግዳለን ብለው ሲታገሉ የነበሩ በርካታ ሃይሎችም በሰላም ወደ አገራቸው ገብተው ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉም አስችሏል። አሁንም የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ዜጎች በፖለቲካው ዘርፍ የየራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል፡፡

ዜጎች በአገራቸው ሲደርስባቸው የነበረውን እንግልትና ክብረ-ነክ ተግባር ከመቀልበስ ባለፈ፤ “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ…” እንዲሉ፤ በወቅቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን በበርካታ አገራት ለእስርና እንግልት እንዲሁም  ለከፋ ስቃይ ይዳረጉ የነበረበትን ታሪክ መቀየር ያስቻለ ተግባርም አከናውኗል፡፡ በዚህም ብልጽግና ከጎረቤት አገራት እስከ ባህረ ሰላጤው የአረብ አገራት በእስርና እንግልት ያሉ ዜጎች የነጻነት አየር እንዲተነፍሱና ለአገራቸው እንዲበቁ ማድረግ የቻለ የዜጎች ፓርቲ ነው፡፡

በሱዳን፣ በግብጽ፣ በሳዑዲ አረብያ፣ በዱባይ፣ ወዘተ. አገራት ለእስርና እንግልት ተዳርገው የነበሩ፤ በሚደርስባቸው ችግርም ተስፋ ቆርጠው የቆዩ ዜጎች የእዳ ደብዳቤያቸው ተቀድዶ ከተስፋ መቁረጥ ወደ ተስፋቸው ኢትዮጵያ ለመመለስ በቅተዋል፡፡ የፓርቲያችን ሊቀመንበር የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ከእስር ያስፈቷቸውን ወገኖች በተጓዙበት አውሮፕላን ሳይቀር ጭነው በመምጣት የብልጽግናን ሰው አክባሪነት፤ ዜጎች የጥቅም መደራደሪያ ሳይሆኑ ለኢትዮጵያ አስፈላጊና ውድ ስጦታዎች መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡

በብልጽግና ዘመን የተወሰዱ ይሄን መሰል እርምጃዎች እና የተከናወኑ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ዜጎች በያሉበት ኮርተውና ተከብረው እንዲኖሩ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ ተከብረው መኖር ብቻ ሳይሆን በአገራቸው ጉዳይ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ለመደመጥ በቅተዋል፤ ከቀደመ የባይተዋርነት ስሜት ተፋትተው ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ የሚችሉትን ማበርከት ጀምረዋል፡፡ ለዚህም ነው ብልጽግና የዜጎች ክብር ከአገር ክብርና ሉዓላዊነት ተነጥሎ የማይታይ፤ ለዜጎች ክብር መስጠት የአገርን ሉዓላዊነት አስጠብቆ እንደመኖር ሁሉ ውጤት ነው ብሎ የሚያምነው፡፡

ብልጽግና  እንደ አገራዊ ፓርቲ በአዲስ መልኩ ራሱን ሲያደራጅ ሁሉም ዜጋ በአገሩ ጉዳይ እኩል ሚና ሊኖረው ይገባል በሚል እምነት ነው፡፡ የመደመር መንገድን ቀይሶ ጉዞውን ሲጀምርም በኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ባለቤት፣ ማንም ደራሽ እንግዳ ወይም አልፎ ሂያጅ የለም በሚል ሲሆን፤ የብልጽግና ወደ አገር መምራት መምጣት ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች ሁሉ እኩል ክብርና ዋጋ የሚሰጣቸው እንጂ አንደኛው ተመልካች ሌላኛው ደግሞ ወሳኝ መሆን እንደማይችል በተግባር ያረጋገጠበት ነው፡፡

ይህ ደግሞ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አገራቸው እኩል እንደምትፈልጋቸው ሁሉ፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን አስተዳድራለሁ የሚል ፓርቲም ይሄን ታሳቢ አድርጎ መስራት እንዳለበት ብልጽግና በተግባር ያሳየበትና ያስተማረበት ነው፡፡

ብልጽግና ኢትዮጵያ በውጭ ካሉ ዜጎቿ ጋር እንድትራራቅ ብቻ ሳይሆን እንዳትተያይ ተጋርዶ የነበረውን የግንብ መጋረጃ አፍርሶ፤ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ጋር በቀላሉ የሚገናኙበትን ድልድይ መገንባት የቻለ ፓርቲ ነው፡፡ ብልጽግና ከዚህም በላይ በየአገሩ ዜጎች አሉኝ ብሎ ተዘዋውሮ ከያሉበት  ፈልጓል፤ አናግሯል፣ ባሉበት አገር ጭምር እንደ ሰው እንዲታዩና እንዲከበሩ አድርጓል። ስሜታቸውን አዳምጦ ለመረዳት ሞክሯል፣ ጥያቄዎቻቸውን ይዞ ለመመለስ ሰርቷል፤ ስለ አገራቸው ያገባኛል እንዲሉም የቤት ስራ ሰጥቶ ስለ አገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ተቆርቋሪነት እንደየፈርጁ ለይቷል፤ ይህንንም መሰረት አድርጎ እንደየስሜታቸውና ፍላጎታቸው እንዲሳተፉ አድርጓል፡፡

በአጠቃላይ ብልጽግና በለውጡማግስት በይፋ ህዝብን ይቅርታ በመጠየቅ የጀመረው ጉዞ፤ ፖለቲካ ያለ ዜጎች ክብርና ልዕልና ትርጉም አልባ መሆኑን ያመላከተባቸውን በርካታ እርምጃዎች ወስዷል፡፡ በሺዎች ከእስር ሲፈቱ፤ በርካቶች ከስደት ተመልሰዋል፡፡ አዲስ በነደፈው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው አማካኝነት በሰራው የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አገራት እስር ላይ የነበሩ ዜጎች ተፈተው ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ዜጎች በኢትዮጵያዊነታቸው እንዲኮሩ አድርጓል፡፡

በዚህም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለይም እምብዛም ትኩረት ተነፍጓቸው የቆዩት በአረብ አገራት የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ክብራቸው እንዲጠበቅ፤ መብታቸው እንዲከበር እና በማንነታቸው ሳይሸማቀቁ ቀና ብለው እንዲሄዱ ሆኗል፡፡ በተለያየ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸው ካሳ እንኳን ሳይሰጣቸው በከፋ እንግልት ውስጥ ያሉ ወገኖችን በበደላቸው አካል ካሳ እንዲከፈላቸው ተደርጎ ለአገራቸው በቅተዋል፡፡

እዚህጋ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ የሰው ልጅ በአገሩ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የዓለም ክፍላተ አገራት ተንቀሳቅሶ ሰርቶ መለወጥን፤ የተሻለ ኑሮ ማግኘትን መሻቱ ተፈጥሯዊ ባህሪው ነው፡፡ ይህ ሲሆን  የተሻለ ኑሮ ለማግኘት ባለ ፍላጎት ምክንያት ክብርን ዝቅ አድርጎ፤ በማንነት አንገት ደፍቶ ሊሆን አይገባውም፡፡ ብልጽግና  የሰራውም፣ እየሰራ ያለውም ሆነ ወደፊት የሚሰራው ዜጎች በያሉበት ቦታና አገር ክብራቸው ተጠብቆ፤ በማንነታቸው ሳይሸማቀቁ አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ በማስቻል በሁለንተናዊ አገራዊ ብልፅግና ጉዞው ተሳታፊና የስኬቱም ባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል ነው፡፡ ስለዚህም በሁሉም ስፍራ ለሚገኙ ዜጎቻችን ክብርና ልዕልና በቁርጠኝነት፣ በታማኝነትና በታታሪነት እየሰራ ያለውን ብልጽግና ይምረጡ፡፡

እኛ ብልጽግና ነን!!

Loading

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *