ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ያደሩ የቤት ስራዎቸ አሉ። እነዚህን ለይቶና በቅደም ተከተል አቅዶ የመተግበር አስፈላጊነት አጠያያቂ አይሆንም። ለዚህም ነው ፖለቲካው ሲታመም የተገራገጨውን ኢኮኖሚና ለዓመታት ሲንከባለል የመጣው ማህበራዊ ቀውስ በፍጥነት ታቅዶ መስመር ካልያዘ ለአገር አደገኛ መሆኑን የለውጥ ኃይሉ በመገንዘብ ጊዜ ሳይወስድ አፋጣኝ መፍትሄ የሰጠው። ስለሆነም የለውጥ ኃይሉ ሁሉንም ለመፍታት ማቀድ፣ ያቀዱትን ተግባራዊ ለማደረግ መንቀሳቀሱን ቀዳሚ ተግባሩ አደረገ።
የለውጥ ኃይሉ ዓላማውን በግልጽ ለማሳወቅና የህዝቡን ሙሉ ድጋፍ ለማግኘት በክልሎች መንቀሳቀስ የመጀመሪያው እቅዱና እርምጃ መሆን ነበረበትና ለህዝቦች በፍጥነት የለውጡን ዓላማና ግብ በየመደረኩ ገለጸ። ወደፊት ሊሰራቸው ያሰባቸውን አሳወቀ። ለውጡ ተቀጣጥሎ ውጤት ሲያመጣ በከፍተኛ ድምጽ በሊቀመንበርነት የተመረጡት የፓርቲያችን ሊቀመንበር ዶክተር ዓብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲሰየሙ ለህዝብ ቃል የገቡትን በተግባር እንደሚተረጉሙ ከህዝቦች ጋር በቀጥታ ባደረጉት ውይይትም አጸኑ።
የፖለቲካ እሰረኞች ተፈቱ። የታፈኑ መገናኛ ብዙሃን ነጻነታቸውን አገኙ። በውጭ በስደት ላይ የነበሩ ፖለቲካኞች የቆሙለትን ዓላማ ያንጸባርቅልኛል ያሉትን አርማ እያውለበለቡ፣ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ በደጋፊዎቻቸው ታጅበው አዲስ አበባ ገቡ። ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ በህዝብ ፊት ቃል ለመግባት የቻሉት የለውጥ ሃይሉ ያለውን ለመፈጸም ቁርጠኛ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ስላልነበራቸው ነው። ይህ የመጀመሪያው እቅድ የተግባር ውጤት ነበር።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለዓመታት ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት ያስቀጠለው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የሚመራ የልዑካን ቡድን ኤርትራን በጎበኘበት ወቅት ነበር። በተለይም “ጦርነት የለም፤ ሰላምም የለም” በሚል ሁኔታ ለዓመታት በውጥረት የቆየውን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ ሰላም በማምጣት የለውጥ ሃይሉን የመጀመሪያ ትልቅ እቅድ አሳክቷል። ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚኖርን ግንኙነት በመከባበርና በመረዳዳት፣ በመደመር ስሜት እንዲሆን በማቀድና በመተግበር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ተችሏል።
በለውጡ ዘመን ኢትዮጵያ ለዜጎችና ለዲፕሎማሲ ልዩ ትኩረት ሰጥታ ተንቀሳቅሳለች። የአገራችንን ተሰሚነት የሚጨምሩና አገራዊ ክብርን ከፍ የሚያደርጉ ተግባራት በእጭር ጊዜ ውስጥ ተከናውነዋል። በተለያዩ አገሮች ጉብኝት በማድረግ የለውጡን ዓላማና ግብ በግልጽ ለማስረዳት ተችሏል፤ በዚህም መልካም የሆነ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተፈጥሯል። አገሮቹ በየራሳቸው መንገድ ለለውጡ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
ብልጽግና በየአገሩ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማነጋገር፣ ለአገራቸው በጉልበታቸወ፣ በእውቀታችውና በገንዘባቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ያደረገ፣ ለተፈጻሚነቱም ሁኔታዎችን አመቻችቶ ውጤት ያስገኘ ፓርቲ ነው። የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዓብይ “ግንቡን እናፍርስ፤ ድልድዩን እንገንባ” በሚል መርህ በአሜሪካና በአውሮፓ አገራት ያደረጉትን ጉብኝትና የተገኘውን ውጤት እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል።
ብልጽግና የዜጎች ክብርን መሰረት በማድረግ ዲፕሎማሲውን ከፍ ያደረገ ፓርቲም ነው። ፓርቲያችን በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ዜጎቻችን በኢትየጵያዊነታቸው ታፍረውና ተከብረው እንዲኖሩ ማድረግ ዋነኛ ግቡ አድርጎ ተንቀሳቅሷል። ውጤትም አስመዝግቧል። ለአብነት ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ምክንያቶች በሰው አገር እስር ቤት ሆነው ሲሰቃዩ ፈጥኖ በመድረስ እንደ ገዥ ፓርቲነቱ ያለበትን ሃላፊነት በብቃት ተወጥቷል። በዚህም ከ40 ሺህ በላይ እስረኞች ተፈተው ወደ አገራቸውና ቤተሰቦቻቸው ተመልሰዋል። በሕገወጥ መንገድ ከአገራቸው ወጥተው ሲሰቃዩ የነበሩ 200 ሺ የሚሆኑ ዜጎች በፍጥነት የጉዞ ሰነድ ተዘጋጀቶላቸው የአገራቸውን ምድር መርገጥ ችለዋል። አቅዶ በመፈጸም ለዜጎች ክብር የቆመ ፓርቲ ነው ስንልም ይህንንም ጉዳይ በዋቢነት በመጥቀስ ነው።
በሶስት ዓመት ውስጥ በአገሪቷ በማህበራዊ ልማት ቀላል የማይባል ለውጥ ማስመዝገብ የተቻለው ባቀደው መሰረት መንቀሳቀስ የቻለው ብልጽግና ፓርቲ ሥራውን በብቃት ስለመራው ነው። ለትምህርት ዘርፍ ፓርቲው የሰጠው ትኩረት ለዚህ አብነት ነው።
በትምህርት ዘርፉ የነበረውን ችግር ለማረም የወሰዳቸው እርምጃዎች እስከዘሬ ድረስ ተደርጎ የማይታወቅ ስለመሆኑ ምሁራን፣ ወላጆችና መምህራን በተለያዩ መድረኮች የመሰከሩለት ነው። የትምህርት ፍኖተ ካርታ ሲወጣ ባልተለመደ መልኩ ህዝብ እንዲወያይ መደረጉም ለህዝብ አሳታፊነታችን ተጠቃሽ ነው። በትምህርት ፍኖተ ካርታው በፌዴራልና በክልል ደረጃ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተወያይቶ ሀሳብ አዋጥቷል። በዚህም ፍኖተ ካርታው አገራዊ፣ ዓለማቀፋዊ ፍላጎቶችና እይታዎችን እንዲያሟላ ተደርጎ ለመቅረጽ ተችሏል።
ብልጽግና ፓርቲ በትምህርት ዘርፍ ስትራቴጂካዊ ለውጦች ለሚያመጡ ተግባራት ልዩ ትኩረት በመስጠት ተንቀሳቅሷል። ትምህርት በፍትሃዊነት ተደራሽ እንዲሆን የትምህርት ቤት ግንባታዎችን አቅዶ በመፈጸም ያስመዘገባቸው ስኬቶችም ለቀጣዩ ስራ ታላቅ ስንቅ አድርጎ ይወስዳቸዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በእቅድና በተግባር የሚያምን፣ በስራና ውጤት ላይ የሚመረኮዝ መሆኑን በመሆኑ ኮቪድ 19 ቫይረስ የዓለም ፈተና ሆኖ ሲመጣ በተረጋጋ ግን ከአገራችን ተጨባጭ ጋር የሚዛመድ ፈጣንና ፍቱን የሆኑ እርምጃዎችን በመውሰድ የከፋ አደጋ እንዳይከሰትና አገርና ህዝብ አደጋ ላይ እንዳይወድቁ ማድረግ ችሏል።
ቫይረሱን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመግታት በማዕከል የሚመራ ብሄራዊ ግብርኃይል በማቋቋም ወደ ተግባር መግባቱ በሽታው ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳትና ተጽእኖ ለመቋቋም ትልቅ አቅም ሆኗል። በአጭር ጊዜ ውስጥ በዓለምአቀፍ ደረጃ አዳዲስ የማከሚያ፣ የለይቶ ማቆያ፣ የህክምና የላብራቶሪ አገልግሎት በማዘጋጀትም የህዘብን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን ተወጥቷል። በዚህ ደረጃ ችግሩን ለመቋቋም መቻሉ ብልጽግና እንደገዥ ፓርቲ ትክክለኛ አቅጣጫ ነድፎና አቅዶ እንደሚንቀሳቀስ ህያው ምስክር ነው። ከዚህም በላይ ፓርቲው በስራዎቹ ለውጤት እንደሚጨነቅ በፈተና ወቅት ጸንቶ በመቆም ቸግሮችን አንደአመጣጣቸው እንደሚመልስ በግልጽ ያሳየበት አጋጣሚ ነው።
ፓርቲው ለዓመታት ተከምረው የቆዩትን የቤት ስራዎች በእቅድ ለመወጣት ሲሞክር እንቅፋቶች አላጋጠሙትም ማለት አይቻልም። በጸረ ሰላም ኃይሎች አነሳሽነት እዚህም እዚያም የሚደርሰው ግጭት፣ አገርን አደጋ ውስጥ የከተተ ክህደት፣ የዜጎች ከኖሩበት አካባቢ መፈናቀልና መሰደድ ከባድ ፈተናዎች ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ድርቅ፣ ጎርፍና የአንበጣ መንጋ የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ ችግሮችም እጅግ ፈታኝ ነበሩ። ይሁንና ብልጽግና በእያንዳንዱ እርምጃ ፈተናዎች ሊኖሩ አንደሚችሉ አስቀድሞ በመገመትና እንደየአመጣጣቸው ሰከን ያለ የመፍትሄ አቅጣጫ በማሰቀመጥ የከፋ ችግር እንዳያስከትሉ ለማድረግ ችሏል።
ለዚህም ነው ፓርቲያችን በምንም ችግር ውስጥ ይለፍ ያቀደውን ይፈጽማል የምንለው። ከላይ ከጠቃቀስናቸው ጉዳዮች በተጨማሪ የሸገር ፕሮጀክት እንዲሁም የእንጦጦና አንድነት ፓርኮችም ፓርቲያችን ብልጽግና ቃሉ ተግባር የሆነ ፓርቲ እንደሆነ የሚመሰክሩ ህያው ማስረጃዎች ናቸው።
ፓርቲያችን እነዚህን ታላላቅ ፕሮጀክት አቅዶ ተፈጻሚ ሲያደርግ ተዝረክርከው የቀሩና የተጓተቱ ብሎም ወደ መቆም ደርሰው የነበሩ የአገር አርማ የሆኑ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመለየትና የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድም ጭምር ነው። ከዚህ አንጻር በዝርፊያና የአስተዳደር ቸግር የተነሳ ወደ መቆም ተቃርቦ የነበረውና ብልጽግና ደርሶ የታደገውን ታላቁ የህዳሴ ግድባችንን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል።
እነዚህንና ሌሎች ስራዎችን ስንመለከት ፓርቲው ያቀደውን ለመፈጸም ብቃት እንዳለው ይመሰክራል። በብቃት አቅዶ በብቃት መፈጸም ደግሞ ጊዜው የሚጠይቀው መሰረታዊ መመዘኛ ነው። በዚህ ተፈትኖ ውጤት ያስመዘገበውን ፓርቲ ለመምረጥ ምን ያህል ተዘጋጅዋል? የነገይቱን ኢትዮጵያ ብልጽግና ለማየት ዛሬ ላይ ነገን የሚገነባውን ፓርቲ መምረጥ ትውልድን መታደግ ነው። ’’ብልጽግናን ይምረጡ” ስንል አቅዶ በመፈጸምና ተጨባጭ ውጤት በማስመዝገብ ያምናሉ እያልንዎት ነው።
እኛ ብልጽግና ነን!
![]()
