ብልጽግና – የሴራ እና የመጠላለፍ ፖለቲካን በሀሳብ ልዕልና ድል የነሳ ፓርቲ!

የኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ዓመት ታሪክና ስልጣኔ ባለቤትነት፣ ያልተቆራረጠ የመንግስት አስተዳደር ስርዓት እንዲሁም የአገረ መንግስት ግንባታ ያላት አገር ናት የምንለው ለዚህ እውነታ በርካታ አብነቶችን ማቅረብ ስለምንችል ነው፡፡ እንደ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ፋሲለደስና የጀጎልን ስነህንጻ ጥበቦችን አጣቅሰን፤ የራሷን የቀን አቆጣጠርና ፊደል ቀርጸው ያለፉ ጠቢባንን እማኝ አድርገን፤ ለዲሞክራሲ ስርዓት እውን መሆን እድሜ ጠገቡን የገዳ ስርዓትና ሌሎችንም አያሌ የኢትዮጵያውያን ቱባ እውቀቶችና ስልጣኔዎችን በጉያችን ይዘን ነው፡፡

ያልተቆራረጠ የአገረ መንግስት ግንባታችን እና የፖለቲካ ጉዟችንም እኛ ኢትዮጵያውያንን የህያው ታሪክ ባለቤት አድርጎናል፡፡ ይህ ማለት ግን የዘመናት የታሪክ ሂደታችን ሁሉም እንከን አልባ ሆኖ የተጓዘ ነው ማለት አይደለም፡፡ በተለይ ከዘመነ መሳፍንቱ መገባደጃ ጊዜ ጀምሮ የነበረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ በሴራ እና መጠላለፍ እየተቃኘ ለመምጣቱ አያሌ ማሳያዎች ይነሳሉ፡፡

ያ ወቅት ፖለቲካው ከመተባበር ይልቅ መገፋፋትን፤ ከመደጋገፍ ይልቅ መጠላለፍን፤ ከሰላማዊ ውይይትና ድርድር ይልቅ መጠፋፋትን እንደ አማራጭ አድርጎ የያዘበት ነበር፡፡ የኢትዮጵያን የመንግስት አካሄድም ባለው ላይ እየደመሩ ከማራመድ ይልቅ ሁሉንም እያፈረሱ ከዜሮ በመጀመር ሁሉም የራሱ ባለታሪክ የመሆን አካሄድን መረጡ፡፡ ለዚህ ደግሞ የአፄ ኃይለስላሴና የደርግ ውድቀትን ተከትሎ የሆነው አንድ ማሳያ ሲሆን፤ በመፈንቅለ መንግስት ታግዞ ስልጣን የያዘውን ደርግ በተመሳሳይ ሴራ በኢህአዴግ መወገዱ የፖለቲካችን ሴራና መጠላለፍ ዓብይ ገጽታ ነው፡፡

ከዚህ በኋላ የመንግስት ስልጣኑን የተቆጣጠረው ህወሓት መራሹ ኢህአዴግም የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደላቀ ሴራ እና መጠላለፍ አሳደገው፡፡ አካሄዱን በረቀቁ የህግ አሰራሮች አግዞ ከፖለቲካው አልፎ በህዝቦች መካከል መከፋፈልና አለመተማመንን ለመፍጠር ቀን ከሌት ሰራ፡፡ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሌሎችም በሀሳብ ልዩነታቸው ተቀጽላ ስም ተሰጣቸው፤ ከአገር አንዲሰደዱ ተደረገ፤ ታሰሩ፣ ተገረፉ፣ በጨለማ ቤት ዓመታትን አሳለፉ፤ አካላቸውን እና ህይወታቸውንም አጡ፡፡

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያውያንን ለከፋ አፈናና ጭቆና፤ ኢትዮጵያንም ለደህንነት ስጋት ዳረጋት፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ሊከፋፍሏትና ሊያጠፏት የሚያሴሩ እንዳሉባት ሁሉ፤ ለህልውናዋና ቀጣይነቷ የሚተጉ ልጆች ያላጣች ናትና ይሄን የሴራና የመጠላለፍ ዘመን የሚቀለብስ፤ ለሃሳብ ልዕልና ቅድሚያ የሚሰጥ ፓርቲ እውን የሆነበት ለውጥ መጣ፡፡ ለውጡም ብልጽግናን ወለደ፡፡ ብልጽግናም በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ባለችው አገራችን ከየትኛውም ጽንፍ ሳይወግን ችግሮችን ተቋቁሞና መስዋዕት ከፍሎ ኢትዮጵያን ለማሻገር ቆረጠ፡፡

እናም በኢትዮጵያ የነበረውን ኢፍትሃዊ ተሳታፊነትና አካታችነት የጎደለው አካሄድ በመለወጥ ሁሉም እኩል የሚሳተፍበትና የሚወከልበትን እድል በመፍጠር በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ ችግሮችን መፍታት ቻለ፡፡ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል እውነተኛ ፌዴራሊዝም ለመትከል ሰራ፤ ሁሉም በፍትሃዊ መንገድ የሚወከልበትና አካታች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠርም በትጋት ተንቀሳቀሰ፡፡ በዚህም አያሌ የህዝብ ጥያቄዎችን መመለስ፤ የፖለቲካ ድባቡንም መቀየር ቻለ፡፡

በዚህም በአገራችን ስር ሰድዶ የቆየው ሴራ እና የመጠላለፍ ፖለቲካ የፈጠረውን የጥቂቶች የበላይነት እንዲወገድ ብልጽግና መሰረት ጥሏል፡፡ ያለ ፍርድና ያለ ህግ በፖለቲካዊ ሴራና በጥቂቶች አምባገነንነት ሰዎች እንዳይታፈኑ፣ እንዳይገደሉና ነፃነታቸውን እንዳያጡ የህግ ሪፎርም ማድረግም ችሏል፡፡ በፖለቲካ አመለካከታቸው እና በሀሳባቸው የተነሳ ጽንፈኛ፣ አሸባሪና ሌሎችም ቅጥያ ስሞች ተሰጥቷቸው ከአገራቸው የተሳደዱ፤ ለረጅም ዓመታት ወደ አገር ቤት መግባት ያልቻሉ ዜጎቻችን በነፃነት መግባትና መውጣት እንዲችሉ አደረገ፡፡

እነዚህና ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያን ከሴራ ጉዞ እና ከመጠላለፍ ፖለቲካ ያላቀቁ እርምጃዎች የወሰደው ብልጽግና፤ በእነዚህ እርምጃዎቹ ውጤት ማምጣት ጀምሯል፡፡ በቀጣይም አሁን ለሚታዩ ችግሮችም መፍትሔ ማምጣት የሚያስችል ሙሉ ተነሳሽነቱም፣ አቅሙም ያለው ፓርቲ መሆኑም በተግባር ታይቷል፡፡

በብልጽግና ዘመን የአፈና አካሄድ ቀርቷል። በአመለካከታቸው የሚገፉ የፖለቲካ ኃይሎች ታቅፈዋል፤ የተሰደዱት ተመልሰዋል፤ የታሰሩ ተፈትተዋል፤ አጋጅ ህጎች ተሻሽለዋል፣ ተለውጠዋልም፡፡ አሁን እዚህም እዚያም የሚታዩ ችግሮችና ያደሩ የቤት ስራዎች አሉ፤ እነዚህ ግን ብልጽግና ተግቶ የሚሰራባቸውና ነገ የሚፈቱ ናቸው፤ ብልጽግናም ይሄን የሚያደርግ ፓርቲ ነው፡፡

ምክንያቱም ብልጽግና በሁሉም ልብ ውስጥ ተዳፍና የምትብላላውን ኢትዮጵያ ከፍ አድርጎ ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያነቃነቀ፤ የመደመር ፍልስፍናን በማምጣት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በይቅርታና መደጋገፍ ላይ ተመስርቶ በሀሳብ ልዕልና እንዲያምን ተግቶ የሰራና የሚሰራ ፓርቲ ነውና፡፡ የአገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን የቀጣናውን ፖለቲካ የሚቀይር እርምጃ ወስዶ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካለል የሰላም አየር እንዲሰፍን ያደረገ፤ ሌሎችም የማይደፈሩ የሚመስሉ ውሳኔዎችን ጭምር በመወሰን ከፍተኛ ስራዎችን ያከናወነ ፓርቲም ነው ብልጽግና፡፡

ብልጽግና ኢትዮጵያዊነትን ከማንነት ጋር አስተሳስሮ የሚያስኬድ፤ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርና በአስተዳደራቸው ቋንቋቸውን ከመጠቀም ባለፈ ወደ ፌዴራል የማሳደግ እድል የሚሰጥ፤ የጋራ የሆነችውን ኢትዮጵያንም በባለቤትነት ስሜትና በእኩል ተሳትፎ ማልማትና መገንባት እንዲችሉ እየሰራ ያለ፤ ኢትዮጵያዊነትን ከማንነት ጋር አስተሳስሮና አጣጥሞ የሚያስኬድ፤ ኢትዮጵያን ከፖለቲካ ሴራ እና ከመጠላለፍ ጉዞ ለማላቀቅ እየሰራ ያለ፤ በቀጣይም በቁርጠኝነት የሚሰራ ነው፡፡

ከአገራዊ ለውጡ ማግስት በተለይም የብልጽግናን እውን መሆኑን ተከትሎ በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል። ለዘመናት የፖለቲካችን አይነተኛ መልክ የሆነው የሴራ እና የመጠላለፍ ፖለቲካንን ለመቀየር በብልጽግና ዘመን እርምጃዎች ተጀምረዋል። ለዚህ ማሳያው ደግሞ በአገር ውስጥ በሰላም ሲንቀሳቀሱ የኖሩት ብቻ ሳይሆኑ፤ የተለያየ ታርጋ ተለጥፎላቸው ላይመለሱ ከአገር እንዲሰደዱ የተደረጉ የፖለቲካ ኃይሎች እንዲሁም በትጥቅ ትግል ቆይተው በሰላም ለመታገል ወደ አገር ውስጥ የገቡ ቡድኖች ሳይቀሩ በነጻነት እዲሳተፉ መደረጉ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የፖለቲካው ምህዳር ሴራ እና መጠላለፍ በአንድ ጀንበር የአመለካከት ለውጥ የሚመጣበት እና ሁሉም ነገር የተስተካከለ ላይሆን ይችላል፡፡ ዋናው ጉዳይ ከዚህ ችግር ለመውጣት ሁሉም ራሱን አሳምኖ መስራት እና በዚያው ልክ ቁርጠኛ ሆኖ መንቀሳቀስ መጀመሩ መቻሉ ሲሆን፤ ይሄን አይነት ልምምድ ሲዳብር ሴራው ቀርቶ መልካምነት፤ መጠላለፉ ተወግዶ መተጋገዝና መደጋገፍ ቦታውን መያዙ አይቀሬ ነው ብሎ ብልጽግና ያምናል፡፡ ብልጽግናም ይህ እንዲሆን በጽኑ የሚያምን፣ ለዚህ እውን መሆንም ተግቶ የሰራና ውጤት ማሳየት የቻለ፤ አሁንም እየሰራ ያለና በቀጣይም የሚሰራ ፓርቲ ነው፡፡

ወቅቱ የምርጫ ቅስቀሳ የሚደረግበት እንደመሆኑ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች ሁሉ የቀደመውን የመወቃቀስ፣ የመጠላለፍና አንዱ ሌላውን ለማስወገድ በሚያስችል የተንኮል መረብ ከመዘርጋት ወጥቶ በቀና ልብ ለህዝብና ለአገር የሚበጁ ሀሳቦችን ማንሸራሸር ላይ ማተኮርን መለማመድ እንደሚጠበቅባቸው ብልጽግና በጽኑ ያምናል። የሚጠበቅበትን ሁሉ በብቃት ለመወጣትም ትኩረት ሰጥቶ ይንቀሳቀሳል።

ብልጽግና ገና ከጅምሩ ያሳየው የአቃፊነት፣ የፍቅርና ይቅር ባይነት፤ የአሳታፊና የሃሳብ ብዝሃነት አክባሪነት፤ በኢትዮጵያ ሥር ሰድዶ የኖረውን የሴራ ጉዞ እና የመጠላለፍ ፖለቲካ ስልት ከመሰረቱ ለመቀየር ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች ነው፡፡ በዚህም ያመጣቸው አበረታች ውጤቶች የበለጠ እዲጎለብቱ ያለመታከት ይሰራል፡፡

ብልጽግና እስከአሁን ያሳያቸው ጅምሮች በሴራ ጠልፎ ከመጣል ይልቅ በሃሳብ ልቆ ማሸነፍን መርሁ አድርጎ እየሰራ ያለ መሆኑን ያረጋግጣል። በዚህ ተግባሩም ትናት የነበረው መጠላለፍ ዛሬ ተቀይሯል፤ ትናንት የነበረው መሳደድ ዛሬ ታሪክ ሆኗል፤ ትናንት የነበረው እስርና አፈና ዛሬ ተወግዷል፤ እነዚህ ሁሉ የትናንት ጠባሳዎች በይቅርታ መስመር፣ በመደመር መንገድ ተሻግረው የሀሳብ ልዕልናን እርካብ ረግጠው ፈውስ አግኝተዋል፡፡ እናም ብልጽግናን በመምረጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መገለጫ  በሀሳብ ልዕልና ማሸነፍ እንዲሆን ይፍቀዱ፡፡

እኛ ብልጽግና ነን!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *