ብልጽግና የዛሬና የነገ ፓርቲ!

ወርቅ ከማዕድናት በተለየ በሁሉም ዘንድ የመወደድና የመመረጥ ክብር የተጎናጸፈው፤ ከአፈር መገኘቱ ተዘንግቶ አይደለም። በብርቱ እሳት ተፈትኖ በማለፉ እንጂ፡፡ ብልጽግናም በፈተና ውስጥ ተወልዶ በፈተና ውስጥ እያለፈ የመጣ፣ ወደፊትም ፈተናዎችን በጥበብ እያለፈ የሚቀጥል ከዘመን ጋር ራሱን እያደሰና እየለወጠ የሚሄድ ፓርቲ ነው።  ብልጽግና የዛሬና የነገ ፓርቲ በመሆኑና ብሩህ ተስፋን ሰንቆ ለኢትዮጵያ ልዕልና በመትጋቱ ብዙዎች ተስፋቸውን ጥለውበታል፣ ብዙዎችም በፍቅር አብረውት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

የብልጽግና ጉዞ ከአገራዊ ለውጡ ማግስት የተጀመረ አይደለም፡፡ ያኔ ገና የኢትዮጵያ ህዝብ ጭቆና አንገፍግፎት እንቢታውን ማስተጋባት በጀመረበት ወቅት ጽንሰቱን አደረገ እንጂ! ከውጭ ህዝብ ብሶቱን ገልጾ ሲታገል፣ ብልጽግናም በለውጥ አመራር ሃይሉ አማካኝነት በኢህአዴግ ውስጥ ድምጹን ከፍ አድርጎ አሰምቷል፤ ፊት ለፊት ታግሏልም፡፡ ይህ ግን ለለውጥ ሃይሉ ቀላል አልነበረምና  መገፋት፣ መታሰርና መሳደድ አትርፎለታል። የህዝብን ጥያቄ እንዳያነሳ፣ የለውጥ እቅስቃሴው እንዲቀለብስ የሚያስገድድ ሃይል ከፊቱ ቢደቀንም ራሱን ሰውቶ የብርሃን ፈርጥ ለመሆን በመትጋት  ፈተናውን በድል አልፎ የለውጥ ብርሃንን ለኢትዮጵያ አብርቷል።

አገር ሳይሆን ቡድን፣ ህዝብ ሳይሆን ግለሰብ ጎልቶ የሚገለጽላቸው የጥፋት ኃይሎች በለውጡ ሂደት ያጡትን ዘረፋና ኢፍትሃዊ አገዛዝ ለመመለስ ከለውጡ ማግስት አንስቶ  ብዙ ተግዳሮቶችን ደቅነዋል። ለዚህም ሶስቱን ሰኔዎች መመልከት ሁኔታውን በደንብ ለመረዳት ያስችላል፡፡ በብልጽግና አመራር በመስቀል አደባባይ የተፈጸመው የግድያ ሙከራ፤ ከፍተኛ የክልል አመራሮችን የመግደል ሴራ፤ ታዋቂ ግለሰቦችን በማስገደል ህዘብን ከህዝብ ለማባላት በዚህም አገርን ለማፍረስ የተደረጉ የጥፋትና የሴራ ድግሶች የብልጽግናን የለውጥ ሂደት በማደናቀፍ አገራችንንና ህዝቧን ዳግም ወደጨለማው ዘመን ለመመለስ የተሞከሩ የጥፋት ድርጊቶች ነበሩ። ተላላኪዎችን በማሰታጠቅና የጥፋት ዕቅድ በመንደፍ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ግጭቶች እንዲፈጠሩም አድርገዋል። በዚህም በርካታ ዜጎች በሰላም ከኖሩበት ተፈናቀልዋል። ለስደት፣  ለአካል ጉዳትና ሞትም ተዳረገዋል፤ አያሌ ንብረትም ወድሟል፡፡

እኒህና መሰል የጥፋት ተግባራት የሚፈጸሙት የለውጡ አመራሩ ትኩረቱን ወደ ልማት ሳይሆን ህዝብን ወደማረጋጋት እና መልሶ ማቋቋም እንዲያዞር በማለም ነበር። ነገር ግን በመደመርና በፍቅር ስሜት ህዝብ ከብልጽግና ጎን ነበርና ችግሩንና ተግዳሮቶቹን በማለፍ መሻገር ተችሏል፡፡ ብልጽግና፣ ከለውጡ በፊት በነበረው የአፈና ወቅትም ሆነ በለውጡ ማግስት በጥፋት ኃይሎች በተፈፀመ ጥቃት ተፈናቅለው የነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን መልሶ አቋቋሟል።

እኛ ብልጽግናዎች ከጅምሩ ለህዝብ “እንሰራለን” ብለን ነበርና የህዝብን ድምጽ ለመስማት በየቦታው ተዘዋውረን ከህዝብ ጋር መክረናል። በመድረክ የገባነውን ቃል በመጠበቅ ከሂደታችን ሳንገታ በሰራናቸው ተከታታይ አገራዊ እና ቀጣናዊ የሰላምና የልማት ተግባራት ፍሬ አፍርተንም ከህዝባችን ድጋፍ ተችሮናል። ከዓለምአቀፍ ተቋማትም አስከ የሰላም ኖቬል የደረሰ ሽልማትን ተጎናጽፈናል፡፡ ይህ ደግሞ የብልጽግናና የሰላም ወዳዱ ኢትዮጵያዊ የጋራ ድምር ውጤት እንደሆነ ብልጽግና አጥብቆ ያምናል፡፡

ከሰው ሰራሽ ተግዳሮቶች ባለፈም በለውጡ ዘመን ተፈጥሯዊ ቸግሮች የፈጠሩት ፈተና እጅግ ከባባድ ነበር። ለአብነት ያህልም በድርቅ ምክንያትሚሊዮኖች ለከፋ ችግርና ረሃብ የተዳረጉበትን ሁኔታ ማንሳት ይቻላል፡፡ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ በተለያዩ አከባቢዎች ተከስቶም በመቶ ሺዎች እንዲፈናቀሉና በርካታ ዜጎች ቤት ንብረታቸውን እንዲያጡ አደርጓል። የበረሃ አንበጣ መንጋም ቢሆን ደጋግሞ ኢትዮጵያን ጎብኝቷት ድክድክ የሚለውን የአገሪቱን ኢኮኖሚና የአርሶ አደሩን ህይወት ክፉኛ ፈትኗል፡፡ ይሁንና ብልጽግና መላውን ሀዝብ ከጎኑ በማሰለፍ እነዚህን ቸግሮች በጽናት አልፏል።

ዓለምን ጭንቅ ውስጥ የከተታት የኮቪድ 19 ወረርሺኝም ሌላው የለውጥ ኃይሉ ፈተና ነበር። ይህ ወረርሺኝ የዳበረ ኢኮኖሚ ገንብተዋል የተባሉ ታላላቅ የዓለም መንግስታትን ሳይቀር በእጅጉ የተፈታተነ እና ዜጎቻቸውን ለሞት የዳረገ ክፉ ደዌ ነበር፡፡ ብልጽግና ግን እንደ ፓርቲም እንደ መንግስትም ቀድሞ የመከላከያ መንገዶቹን ቀይሶ እና ህዝቡን አስተባብሮ ችግሩን መከላከልም፣ መቋቋምም እንደሚቻል አሳይቷል፡፡

እነዚህና ሌሎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሰው ሰራሽ አደጋዎች በተከሰቱበት ልክና በተፈራው መጠን ጉዳት አላደረሱም፡፡ ይህም የሆነው ብልጽግና ለፈተናዎች ከመንበርከክና ከመበርገግ ይልቅ የፈተና መውጫና ማለፊያ መንገዶቹን በመቀየሱና ከህዝብ ጋር በመምከር እጅ ለእጅ ተያይዞ በመስራቱ የተገኘ ውጤት ነው፡፡

ለውጡ ገና በለጋ ዕድሜ እያለ ውስብስብ የፖለቲካ ትኩሳት በሶማሌ ክልል ተከሰቶ ነበር፡፡ ይህ አገር የማፍረስ የጥፋት ተልዕኮ አንዱ ገጽ ቢሆንምና የለውጥ ሃይሉ ገና ባልጠነከረ ቁመናው ላይ እያለ የተከሰተ ችግር ቢሆንም  ኢትዮጵያን በማሰቀደም ማሸነፍ እና አገርን መታደግ ችሏል፡፡ ይሄ አለመሳካቱ ዳግም ያንገበገባቸው የጥፋት ሃይሎች ታዲያ መሰረታቸውን ሁከትና ግርግር አድርገው በየቦታው እሳት ከመለኮስ አልታቀቡም፡፡ ይሄም የፓርቲያችን ሌላው ፈተና ከመሆኑም በላይ ትኩረታችንን ወደ ልማት ብቻ እንዳናደርግ እና የብልጽግና ጉዞውን ለመግታት ከተሸረቡ ሴራዎች አንዱ ሰበዝ ነበር፡፡

በዚህም ሳያበቃ ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቅና በቀጣይም ትውልድ የማይዘነጋው የህወሓት ጁንታ በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ክህደትና ጥቃት ፈጽሞ አገር የማፍረስ ተግባሩን ገሃድ አወጣ፡፡ ይህ ትልቅ አደጋ ግን ብልጽግናን ተስፋ የሚያስቆርጥ አልሆነም፡፡ ኢትዮጵያውያንም የብልጽግናን አገር የማዳን እርምጃ ተገንዝበው ከጎኑ መሆናቸውን በተግባር አረጋገጡ፡፡ ስለ ኢትዮጵያና ስለ አገር አንድነት ሲሉም በህብር ተሰለፉ፡፡ በዚህም የጥፋት ኃይሉን በአጭር ጊዜ  አደብ በማስገዛት በአገር ላይ የተደቀነውን አደጋ ማስቀረት ተችሏል።

ይህ ሁሉ እውን የሆነው ደግሞ በአንድ በኩል በለውጥ መንፈስ ህዝቡ ከብልጽግና ጎን በመቆሙ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ግን የለውጥ ኃይሉ ቁርጠኛ አቋምና የተቋማት ሪፎርም ስራዎች ድምር ውጤት ነው፡፡ እነዚህን መመልከት ለቻለ ደግሞ ብልጽግና በፈተና ውስጥ ሆኖም ነገን ማየት ብቻ ሳይሆን የታየውን ብሩህ ተስፋ እውን በማድረግ ቃሉን የሚያከብር ፓርቲ  መሆኑን ይረዳል፡፡

ዛሬ ላይ የሰነቅነው ራዕይ አሻግሮ የሚያየው የብልጽግና ወቅትን ነው፡፡ ይህ ተስፋ ጨለማ ከወረረውና ብርሃን ከሌለበት የሚታይ ሳይሆን ጠንካራዋ ህብረ ብሄራዊት አገር ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ከሚያስመዘግቡ አገራት አንዷ ሆና አብዛኛውም መሰረታዊ ችግሮቿን የፈታች እና የተሻለ ትውልድ ያላት አገር መፍጠርን የሰነቀ ነው፡፡

ራዕያችን ቁንጽል አይደለም፤ ከአድማስ ባሻገር ብሩህ ብርሃን የሚታየው እንጂ፡፡ የብልጽግና ጉዞምመዳረሻውን ከአድማስ አሻግሮ የሚመለከት እንጂ በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን የሚጥል አይደለም፡፡ በታላቋ ኢትዮጵያ አምሳያ ትልቁን ምስል የማየት ጥበብን የተካነ ነው፡፡ ለዚህም ነው አገራችን በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚውም፣ በማህበራዊውም መስክ የበለጸገች እና በአፍሪካ ፋና ወጊ ትሆናለች የምንለው፡፡

እናም የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፣ ከችግርህ ፈልቅቆ የሚያሻግርህ የለውጥ ሃዋርያ አያስፈልግህምን?… እናምናለን፣ ይሄን ትፈልጋለህ፡፡ ለዚህም ነው ብልጽግናን ምረጥ የምንለው፡፡ ያየኸው የብርሃን ጭላንጭል ቦግ እንዲል፤ አገራችን ለሁላችንም የምትመች እንድትሆን፤ የብልጽግና ጉዟችን እንዳይሳካ አስረው የያዙንን ሳንካዎች ነቃቅለን እንድንጥል፤ መጪው ጊዜ የጋራችን እንዲሆንና ኢትዮጵያ ገናና ሆና ወደ ልዕልና እንድትመለስ፣ የዛሬ እና የነገ ፓርቲህን ብልጽግናን ምረጥ፡፡

ብልጽግና ፓርቲ!

Loading

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *