ሁሌም ቃላችንን እናከብራለን፤ ለዚህ ቅንጣት ጥርጥር የለንም። በፈተናዎች ብንከበብም፣ በችግር ሸለቆ ውስጥ ብናልፍም፣ ሜዳው ዳገት እንዲሆንብን የሚተጋ ኃይል ቢኖርም ቃላችንን እናከብራለን። እኛ ብልጽግናዎች ቃላችንን ነንና።
ቃል እውቀትንና እውነትን መሰረት ሲያደርግ ጥንካሬ ይሰጣል። ተግባራዊ ለማድረግም አቅም ይሆናል። እኛ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በወንድማማችነት ያስተሳሰሩ የማንነት መገለጫዎች፣ ዓለምን ያስደመሙ ድንቅ እሴቶች፣ ባህልና ወጎች እንዳሉን እናምናለን፤ የእምነታችን ምንጩ እውቀት ነው። ከእነዚህ ድንቅ እሴቶች የተፈለቀቁ መስመሮችን ቀይሰን አሁን ላይ ዛሬን እናጸናለን፤ ዛሬ ላይ ሆነንም ነገን እንገነባለን።
የህዝብን ቁጭትና ፍላጎት አስተውለን፣ ችግሮቹን በጥልቀት ገምግመን፣ ዓለም አቀፍ ሁኔታውን ተንትነን በሀሳብ ስንፋለም፣ ህዝባችን አሁን ያየውን የብርሃን ብልጭታ ነገ ላይ ለሁሉም እኩል የሚፈስ የብርሃን ጅረት ለማድረግ ስንታገል ለራሳችን ቃል ገብተን ነው። ቃላችን የእወቀትና የእውነት መሰረት አለውና ፈጽመነዋል፤ እንፈጽማለንም።
ኢትዮጵያዊያን ትናንት ላይ የቀመሩልንን እውቀት አጢነን፣ የአካባቢያችንን መስተጋብር በጥንቃቄ አስተውለን በመደመር መንገድ እንጓዛለን ብለን ቃል ስንገባ ከሌሎች የተቀዳ ርዕዮተ ዓለም አጥር ሳይሆንብን ራሳችንን ከሁኔታው ጋር እያዛመድን የራሳችንን መንገድ ቀይሰን ወደ ብልጽግና አንጓዛለን ማለታችን ነው። ቤታችን ውስጥ ለዘመናት የተቀመረው፣ በሕዝባችን ዘንድ ያለው ትስስር በእውቀት ከተመራና ደብዝዞ የነበረው የአንድነት መንፈስ እንዲመለስ ከተሰራ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ዋልታና ማገር ስለመሆኑ ጥርጥር የለንም።
እኛ ለሌሎች ርዕዮት አለም ተገዥ አንሆንም ስንል፣ የችግራችንን ሰበዞች ለመፍታት ሀገራዊ መፍትሄ እናስቀድማለን፣ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ ብንማርም ከራሳችን በላይ ለራሳችን እውነት የሚቀርብ የለም ብለንም እናምናለን ማለታችን ነው። ለዘመናት ካካበትነው እምቅ የእወቀት ሀብት ተነስተን ዴሞክራሲን እንገነባለን፤ በግለሰብና በቡድን መብት መካከል ሚዛን አስጠብቀን እንደምንጓዝ ስንናገር ከትናንት የነቀስናቸውን ስህተቶች እንደምናርም በማረጋገጥ ነው።
የአገራችን ኢኮኖሚ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስለመገኘቱ ምስጢር አይደለም። ብልጽግናዎች እውነቱን እንቀበላለን። ይህ ሁኔታ የቀደሙ አባቶቻችንን ታሪክ ስናጤንና በተጨባጭ ስንመረምር ፍጹም ለኢትዮጵያዊያን የማይመጥን መሆኑን አናስተውላለን። በሳል አእምሮዎች ይዘን፣ የሚጠበቡ እጆችን አይተን፣ ያሰቡትን የሚተገብሩ ታላላቅ ዜጎቻችን፣ ኢትዮጵያዊ እሴት ፈጣሪዎች ከጎናችን አድርገን በመደመር መንገድ ተአምር ሰርተን ወደ ከፍታው እንደምንጓዝ እርግጠኞች ነን። በዓለምአቀፍ ደረጃ ጥበብ ውድ በነበረበት ዘመን የአኩስም ሐውልትን ያቆሙ፣ የላሊበላን ሕንጻ የገነቡ የአባቶቻችን ልጆቸ ነንና ተአምር ለመስራት አያቅተንም፤ ቃላችን ነው። ይህንንም በተግባርና በውጤት እናሳያለን።
ብልዕግናዎች ቃላችን₋ነን! ኢትዮጵያን ለማሳነስ እዚህም እዚያም የሚነሱ የሚያሳምሙ፣ ስሜት የሚረብሹ፣ ተግዳሮቶቻችንን ከፍ ለማድረግ የሚፈትኑ ችግሮች ቢኖሩም፤ ትናንት የተጣሉ የቆምንባቸው ጥብቅ መሰረቶች እንደማይናጉ፣ ለዘመናት እንደድርና ማግ የተጋመድንባቸው መተሳሰሪያዎቻችን እንደማይፈቱ፣ እንደክርና መርፌ የተዋሃድንባቸው እሴቶች እንደማይለያዩ እናውቃለን። የሃይማኖት፣የቋንቋና የባህል ልዩነቶች ያሉን ህዝቦች ብንሆንም ብዝሃነታችን የአንድነታችን መሰረትና ውበት መሆኑን አምነን አንድነታችንን እናጠናክራለን። የዛሬ ችግሮቻችን ሁሉ በእውነት ሃያልነት አሸንፈን፣ በጥበብ እንሻገራለንም።
ማነው በምንም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ቃሉን የሚጠብቀውን የሚጠላ? ማነው ቃሉን የከፈጸመ በኋላ በሌላ ቃልኪዳን ወደ ከፍታ ለመውጣት የሚተጋን የማይመርጥ? ማንም። እንግዲያውስ የኢትዮጵያ ህዝብ! ከአንተው እሴቶች ተፈልቅቆ በወጣው የጥበብ መንገድ ወደ ብልጽግና ለመድረስ ብልጽግናን ምረጥ።
እኛ ብልጽግናዎች ነን!
![]()
