“የብልጽግና ጉዞ” – አስታራቂ ትርክት ፍለጋ!!

ባለፉት ሦስት ዓመታት አዲስ ዓይነት የፖለቲካ ትርክት ብቅ ብሏል። የብልጽግና ትርክት። ሀገራችን በአንድነት ጸንታ እንድትቆይ ብቻ ሳይሆን፣ የግለሰቦች ነጻነትና የቡድኖች እኩልነት የወንድማማች እሴትን አቅፈው እንዲተገበሩ የሚሻ ዓይነት ትርክት ነው። ከእኩልነትና ከነጻነት ተቃርኖ የተወለዱት የዘመናት የፖለቲካ ችግሮቻችን በዴሞክራሲና በወንድማማችነት እሴት ባለመደገፋቸው የተባባሱ ናቸው ብሎ ብልጽግና ያምናል።

ከዚህ ቀደም የተፈጠሩ ትርክቶች አስታራቂና የኢትዮጵያን ችግሮች በምሉዕ እይታ ያልዳሰሱ በመሆናቸው ሀገራችን ከአንድም፣ ሁለቴ ሕልውናዋ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ገብቶ ተዓምር በሚመስል መልኩ ተርፋለች። ከእንግዲህ ሦስተኛ እድል ላይኖርን ይችላል።

“ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” በሚል መፈክር የጀመረው የደርግ ትርክት መጀመሪያ አካባቢ ብዙዎችን አስደስቶ እንደነበር አይዘነጋም። የመሬት ለአራሹ ጥያቄዎችን ሲመልስ ሌሎችም የዴሞክራሲና የእኩልነት ጥያቄዎች ቀስ በቀስ ይመለሱ ይሆናል የሚል ተስፋ በሕዝቡ ልብ ውስጥ ጭሮ ነበር። ሆኖም የደርጉ ባለ ሥልጣናት ለዚያ ምንም ዓይነት ዝግጁነት ባለማሳየታቸው ሊጨናገፍ ችሏል። “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለው መፈክር ለጭቆና መሳሪያ ወደ መሆን ሲጀምር ሕዝባዊ ቁጣዎች በያቅጣጫው ይቀጣጠሉ ጀመር። ከደርጉ የሚሰጠው ምላሽ ተቀናቃኞችን የማውደም ዓላማ ሲይዝ፣ መሠረታዊ የዴሞክራሲ መብቶችን ከመንፈግ አልፎ የዜጎች ሰብዓዊ መብት በአደባባይ ሲጣስ ጸቡ ከባለ ሥልጣናቱ ጋር ብቻ መሆኑ ቀርቶ ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› ከሚለው መፈክር ጋር ጭምር ወደ መሆን ተሸጋግሯል።

ይኼም ቀደም ሲል እንቅስቃሴ ለጀመሩ “የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት” አቀንቃኞችና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎችን ያነገቡና “ሕዝባዊ መንግሥት” እንዲቋቋም የሚጠይቁ ፓርቲዎች ትግላቸውን እንዲገፉበት፣ ሕዝቡንም ከጎናቸው ለማሰለፍ ጥሩ መደላድል ሆኗቸዋል። አንዳንዶቹ የከተማ አመጽን ሲከተሉ ሌሎች ደግሞ የበረሃ ትግልን እንደ ስትራቴጂ ተጠቅመው ታግለዋል። በዚያ ፍጭት ውስጥ ከተራዘመ ጦርነትና የእርስ በእርስ ውጊያ ውጭ ሀገራችን የተረፋት አንድም ነገር የለም። “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለው ትርክትም ከደርጉ ጋር እስከወዲያኛው ተሸኝቶ በአዲስ ሥርዓትና በአዲስ ትርክት ተተክቷል።

ኢህአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ከያዘ በኋላ በመንግሥት ደረጃ በስፋት የተነገረው የብሔር ብሔረሰቦች ትርክት የሽግግር ምክር ቤት ተቋቁሞ ሕገ መንግስት ወደ ማርቀቅ ሲሄድ ትርክቱ ይበልጡን ለመግዘፍና ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ሊያገኝ ችሏል። ምንም እንኳን ይሄ የ83ቱ አብዮት ራስን በራስ የማስተዳደር እንቅስቃሴዎችንና ሕዝቦች በመረጡት ቋንቋ በየአካባቢያው አገልግሎት የሚያገኙበትን አሰራር ማስጀመሩ ባይካድም ቀላል የማይባሉ ችግሮችን አብሮ ይዞት መጥቷል። የአስተዳደር ተዋጽዎች፣ የክልል አደረጃጀቶች፣ የፖለቲካ ተሳትፎዎች ከሞላ ጎደል ብዙዎቹ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በብሔር ላይ ያጠነጠኑ በመሆናቸው ምክንያት ትርክቱ ቀስ በቀስ ሥር እየሰደደ መጥቶ ብዙዎች ሁሉንም ነገር በብሔር እኩልነት ስም ብቻ ወደ መመዘን ተሻጋግረዋል። የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች፣ የታሪክ ምልከታ፣ የማህበራዊና ፖለቲካዊ አደረጃጀቶች ከሞላ ጎደል በብሔር መነጽር መታየት የጀመሩት በዚህ ጊዜ ውስጥ ነው።

የእኩልነት ትርክቱ በአንድ በኩል በዴሞክራሲ ባለመደገፉ፣ በሌላ በኩል ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሀገራችንን በእጅጉ ዋጋ አስከፍሏታል። ቡድኖች የራሳቸውን አጥር አጥረው እንዲቀመጡ፤ በመካከላቸው የልዩነት ግድግዳ እንዲቆም እና ‹ሌሎች› የሚሏቸው ዜጎች በየክልሉና በየዞኑ እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው የመኖርና የመሥራት መብታቸውን አደጋ ላይ እንዲወድቅ በር ከፍቷል። በአንድ ክልል ውስጥ ሁለት ደረጃ ያላቸው ዜጎችን ፈጥሯል።

ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ላይ ባለችበት ወቅት በተፎካካሪ ፓርቲዎች ጎራ የሚቀርቡት ሁለት አማራጮች ግማሽ መፍትሔ ከመስጠት የዘለሉ እንዳልሆኑ ብልጽግና ያምናል። ለግለሰቦች ነጻነት የተለየ ትኩረት የሚሰጡ “ነጻነት ተኮር” ፓርቲዎች የቡድን እኩልነትን ችላ በማለታቸው ምክንያት ኢትዮጵያን በ1983 ዓ.ም ላይ ወዳየችው አብዮት ከመግፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም። ኢትዮጵያ የብዙ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና ሀይማኖቶች ሀገር ናት። ለቡድናዊ መብቶቻቸው እውቅናና መከበር ቦታ የማይሰጥ አካሄድ የጊዜ ጉዳይ እንጂ አብዮት ማስነሳቱ አይቀርም።

ከእነዚህ በተጻራሪ የቆሙት ፓርቲዎች ደግሞ የማንነት ፖለቲካ አራማጆች ናቸው። እነዚህ በየብሔራቸው ኮሮጆ ውስጥ ሆነው የጭቆና ትርክትን የሚያቀነቅኑ፣ የኢትዮጵያን ችግር ለጥጠው የእኩልነት ጉዳይ ብቻ አድርገው የሚመለከቱ ሲሆን፣ የሚያቀርቡት መፍትሔ ከቅርጽ ለውጥ በቀር ኢህአዴግ ከተከተለው እምብዛም ያልተለየ ነው። አብዛኛው ኢትዮጵያዊን የሚመለከቱ ጉዳዮች እንደማያገባቸው ሁሉ እንወክለዋለን ለሚሉት ብቻ ማቀንቀናቸው አንድን ሕዝብ እንደ ደሴት ተነጥሎ እንዲኖር መፍረድ ነው ብሎ ብልጽግና ያምናል።

እነዚህን ሁለት የተራራቁና በሁለት አቅጣጫ የሚጓዙ አካሄዶችን አስታርቆ መሄድ ተገቢ ነው የሚለው የብልጽግና ትርክት፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷን የጠበቀች ኢትዮጵያን በመገንባት ያምናል። ይህንንም ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት ባለፉት ሦስት ዓመታት የወሰናቸው ውሳኔዎችና በይፋ በአደባባይ የሚናገራቸው ትርክቶቹ ማሳያ መሆን ይችላሉ። የግለሰቦችን ነጻነት የሚገድቡ ሕጎችና አሰራሮችን አሻሽሏል። ገደቡን አለፏል ካልተባለ በቀር በአሁኑ ሰዓት ግለሰቦች ሐሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብታቸው ሳይሸራረፍ ተግባራዊ ሆኗል። ሚዲያዎች ላይ የተቀመጡ ግልጽና ስውር እገዳዎች መነሳታቸው፣ የፖለቲካ ምህዳሩ በሰላማዊ መንገድ ትግል የሚያደርጉ ፓርቲዎችን የመደራጀትና የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዲጠበቅ መደረጉ ብልጽግና ለዴሞክራሲያዊነት ያለውን ፍላጎት ያሳያል።

የይስሙላ ፌደራሊዝም አብቅቶ ክልሎች አግባብነት የሌለው ጣልቃ ገብነት ሳይኖርባቸው ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ያሉት ከመቼም ጊዜ በበለጠ አሁን ነው። አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ተሳታፊ የሚያደርግ የቋንቋ ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑም ይታወቃል። ይሄ እርምጃ ሀገራዊ እሴቶች አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ እንዲያቅፉ ከሚያደርጉና የወንድማማችነት እሴት በሀገራችን እንዲያቆጠቁጥ ከሚያደርጉ እርምጃዎች መካከል ዋነኛ ነው። ከዚህ ባለፈ ሀገራዊ ተቋማት ገለልተኛነታቸው እንዲጠበቅ ሰፊ ሥራዎች ሲሠሩ ነበር። የፍትህ እና የዴሞክራሲ ተቋማት (ፍርድ ቤት፣ አቃቤ ህግ፣ ምርጫ ቦርድ፣ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን ወዘተ) እና የጸጥታና ደህንነት ተቋማት (የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ብሔራዊ የደህንነት ቢሮ ወዘተ) ከፓርቲ ተጽዕኖ ተላቅቀው የኢትዮጵያን መልክ እንዲይዙ ሪፎርም መደረጉ በማንኛውም ጊዜ ዴሞክራሲያችንና ሀገራዊ አንድነታችን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የመጨረሻ ዘብ ሆነው የሚያገለግሉበት ምዕራፍ ተከፍቷል።  እነዚህ ሁኔታዎች የብልጽግና መንገድ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ይጠቁማል።

የትርክት ለውጥ ሲመጣ በአንድ ጊዜ መሬት እንደማይረግጥ ግልጽ ነው። ነገር ግን የልዩነት ትርክትን በስፋት ሲነዙ የነበሩ እንደ ሕወኃት ያሉ ድርጅቶች በራሳቸው ጊዜ ከሀገራችን የፖለቲካ ገበያ ገለል ማለታቸው በወንድማማች እሴት ላይ የተመሠረተች፣ ዴሞክራሲያዊት፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያ እውን የምትሆንበት ጊዜ እንዲቀርብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *