እኛ ብልጽግና ነን!

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ለውጥን እጅግ በፈለጉበት፣ የመደመር ፍላጎት አጅግ ባየለበት፣ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ይበልጥ ማጥበቅ ባስፈለገበት ፣ የነፃነትና የፍትህ መሻት አየሩን በሞላበት በዚያ ወቅት ለህዝብና ለሀገር ሲባል የሚከፈለውን ውድ ዋጋ ከፍለንና ከህዝባችን ጎን ሆነን ብርሃን ለመሆን ተጸነስን፡፡ የህዝቦች የነፃነትና የኅብረት ፍላጎት በበረታበት በዚያ ፈታኝ ወቅትም ህይወት ዘርተን ተወለድን፡፡ ከህዝቦች የለውጥ ጨረር ጋር ተደምረንም የብርሃን ፈለግ በመሆን ብልጽግናን ዓላማ አድርገን ተከሰትን፡፡

አገር በውጥረት ውስጥ በነበረችበት በዚያን ወቅት የህዝቦች ህመም ስላመመንና ስቃያቸውም ስላሰቃየን በትግል ውስጥ ራሳችንን ከፊት አድርገን እና ከህዝብ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን የለውጥ ጉዞ ጀመርን፤ በህዝብ ተማምነንና የነገን ብርሃን ዓይተን ተለምን፤ በአስቸጋሪው ዘመንም ለመልካም ምግባር ተወለድን፡፡ ያኔ፣ ገዳዮች ፈለጥናችሁ ቆረጥናችሁ እያሉ ሲዝቱብንና በዙሪያችን ያሉም ተስፋ እንድንቆርጥ ሲታገሉን፣ እኛ ግን የሃሳብ ልዕልናና እውነት ሁሌም አሸናፊ ነው ብለን ለህዝባችን ቃል ገብተን ጉዞውን ጀመርን፡፡

ጥቂቶች መጠፋፋትን ሲሰብኩ አንድነት የታየን፤ መበታተንን ሲያስቡ መደመርን የተለምንና ያቀነቀንን፤  መጪው ዘመን ጨለማ ነው ሲሉን አይደለም የአገራችንን መጻዒ ዕድል ብርሃን ነው ስንል ያመላከትን፤ የዜጎችን ሃሳብ ተቀብለን ለአገር ጥቅም ያዋልን፤ ዴሞክራሲ እንዲያብብ መሰረቶችን ያስቀመጥን፤ የጥላቻ መሃንዲሶች ቂምና በቀልን ሲያስተምሩን በይቅርታ መሻገርን አጥብቀን የያዝንና ይህንንም በተግባር እያሳየን የመጣን ነን አኛ ብልጽግናዎች!

የችግሮች መፍቻ ሁሉ የጠብመንጃ አፈሙዝ ነው ተብሎ በሚታሰብበት ወቅት ሰላማዊ መንገድን የመረጥን፤ የአብዮታዊ አስተሳሰብ በገነነበትና የጥላቻ ትርክቶች በነገሡበት ወቅት የህዝባችንን የልብ ትርታ አድምጠን የሰላም ሰንደቅ ያውለበልብንና ወንድማማችነትን ሰብከን የመጣን የለውጥ ኃይሎችም ነን፡፡

ይህ የብልጽግና የለውጥ ኃይል ኢትዮጵያ ከዳር እስከዳር እየገዘፈ የመጣባትን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት፤ የህዝቦቿን ሮሮና ጩኸት ለማስቀረትና ዙሪያዋን ከከበቧት ፈተናዎች በጥበብ ለማለፍ የተከሰተ ነው፡፡ በለውጣችን የተጣላን አስታርቀን፣ የታሰረን ፈትተን፣ በሃሳቡና በፖለቲካ አመለካከቱ የተሰደደና አገሩ የናፈቀችውን ሁሉ ወደ አገሩ እንዲገባ አድርገን፤ የዴሞክራሲ ምህዳር አስፍተን፤ አሳሪ ህጎችን አሻሽለን፣ በዘረፋ ምክንያት ለውድቀት ተቃርቦ የነበረውን ታላቁን የህዳሴ ግድባችንን አርመንና አስተካክለን ለፍጻሜ አቃርበን  ዛሬ ላይ ነገን ብሩህ ለማድረግ የሠራንና እየሠራን ያለን ነን፡፡ እነዚህና ሌሎች ሥራዎቻችን  እውነትም የተለወጥን ብቻ ሳይሆን ሁሌም ለለውጥ እንደምንሠራም የሚያረጋግጡ አንጸባራቂ ሐቆች ናቸው፡፡

ከአሮጌው አስተሳሰብ ራሳችንን እንደ ንስር ለውጠን ስንመጣ፤ ባዶ የገንዘብ ቋት፣ የገዘፈ ሥራ አጥነት፣ የተዛባ የሀብት ክፍፍልና ኢፍትሐዊ ተጠቃሚነት አገራችንን አስሯት ነበር፡፡ ይሁንና ጉዟችን በጥበብ ነበርና ይሄን ፈተና ከወዳጆቻችን ጋር ተደምረን መሻገሪያውን ቀይሰን ስለተጓዝን አገራችንን ሊመጣ ከነበረው ታላቅ አደጋ ታድገናል፡፡ “እኛ የምንሠራውና የምንጥለው መሰረት በቀጣይ የኢትዮጵያን ከፍታ እና ብልጽግና ያረጋግጣል” የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ እኛ ሁሌም ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ የምንተጋ ብልጽግናዎች ነንና፡፡

እኛ ብልጽግና ነን!

Loading

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *