ህዝብን የሚመጥን የትራንስፖርት መሰረተ ልማትን እውን የማድረግ የብልጽግና መሰረታዊ ርዕይ!

የትራንስፖርት ዘርፍ በአገራችን ዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር ከተገነባበት ጊዜ ጀምሮ ያለና ረዘም ያለ ጊዜ ከወሰዱ መንግስታዊ ተቋማት የሚመደብ ነው፡፡ ይህ የረጅም ዕድሜ ባለቤትና የዕድገት መሰረት ዘርፍ ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ግልጽ የትራንስፖርት ዘርፍ ፖሊሲ አልነበረውም፡፡ በዚህም የተነሳ ለህዝባችንና ለአገራችን የሚመጥን የዘመነ ትራንስፖርት መሰረተ ልማትን ከማድረስና ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ሰፊ ጉድለት ታይቶበታል።

ብልጽግና ፓርቲ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ባሳለፋቸው ሶስት ዓመታት የትራንስፖርት ዘርፉን ለመለወጥ የሚያስችሉ በጥናት ለይ የተመሰረቱ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። እንደገዢ ፓርቲነቱ አስጠንቶ ባገኘው ወጤት መሰረት የትራንስፖርት ዘርፍ ፖሊሲ፣ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ፖሊሲ ከነማስፈጸሚያ ስትራቴጂው፣ እንዲሁም የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂ ዝግጅት ተግባራት በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቶ ወደስራ ካስገባቸው በርካታ የትራንሰፖርት ዘርፍ ስራዎች መካከል የሚጠቀሱ አንኳር ስራዎች ናቸው፡፡

ፓርቲያችን ብለጽግና የቀረጻቸውን ፖሊሲዎች ወደተግባር ከማስገባት ባለፈም በአየር ትራንስፖርቱ፣ በባቡር ትራንስፖርት፣ በማሪታይም ዘርፉ፣ በመንገድ ትራንስፖርት፣ እንዲሁም በመንገድ ግንባታ ዘርፎች ዝርዝር የአስር ዓመት እቅድ አዘጋጅቶ በመፈጸም ውጤቶችም ማየት ችለናል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ለዘርፉ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ ከመስራት ጎን ለጎን በትራንስፖርት ዓይነቶች መካከል ቅንጅትና ውህደት ያስፈልጋል ብሎ ያምናል፡፡ ለምሳሌ፣ የአቬዬሽን ዘርፋችን ከመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ ጋር መቀናጀት ይኖርበታል፡፡ የውሃ ትራንስፖርት አገልግሎት (ማሪታይም)፣ እንዲሁም ባቡር ከመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎታችን ጋር መቀናጀት አለባቸው፡፡ የወደብና ሌሎች አማራጮች መስፋት እንዳለባቸውም ያምናል፡፡

ከዚህ አንጻር በሎጂስቲክስ መስኩ እስከ 99 በመቶ እየተጠቀምን የቆየነው የጅቡቲ ወደብን ነው፡፡ ነገር ግን የሎጂስቲክስ ስትራቴጂያችን አማራጭ ወደቦችን የማስፋት ስትራቴጂን መከተል አለበት በሚል ከጎረቤት አገራት ጋር በወንድማማችነት፣ በምክክርና አብሮ በመስራት መንፈስ አማራጭ ወደቦችን ለመጠቀም፤ ያልተከፈቱ ወደቦችም እንዲከፈቱ ለማድረግ ጥረት በማድረጋችን ሶስት አማራጭ ወደቦችን በመጨመር 99 በመቶ የነበረውን የጅቡቲ ወደብ አጠቃቀማችንን ወደ 92 በመቶ ዝቅ ማድረግ ችለናል፡፡ በቀጣይ አስር ዓመታትም አሁን ያሉትን አራት ወደቦች ወደ ሰባት ማሳደግ አለብን የሚል ግብ  ፓርቲያችን አስቀምጦ እየሰራን እንገኛለን፡፡

በብልጽግና እምነት ለአገራዊ ለውጡ ምክንያቶች አንዱ የህዝቦች የመንገድ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ ነው፡፡ ባሳለፍናቸው ሶስት የለውጥ ዓመታትም እንደ ብልጽግና የመጀመሪያ የቤት ስራችን የነበረው በአንደኛው እና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተይዘው በተለያዩ ምክንያቶች የተጓተቱ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በዝርዝር በመለየት ወደስራ እንዲገቡ ማድረግ ሲሆን በዚህም በድምሩ 181 የመንገድ ፕሮጀክቶች በፓርቲያችን ብልጽግና አመራር ወደስራ እንዲገቡ አድርገናል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀጣይ የህዝባችንን ፍትሃዊ የመንገድ ተደራሽነት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እስካሁን አገሪቱ ከተጓዘችበት ከአንድ የፌዴራል ተቋም (ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን) የሁሉም ክልሎች የመንገድ ጥያቄዎች እንዲመለሱ የማድረግ አካሄድን በመከተል የህዝባችንን ሰፊ የሆነ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንደማይቻል ብልጽግና ፓርቲያችን ይገነዘባል።

በመሆኑም ይሄንን መቀየርና ለህዝባችንም ይበልጥ ለመድረስ ከዚህ ቀደም እንደነበረው የአስፓልት መንገዶች ግንባታን ከፌዴራል አንድ ተቋም ለክልል የሚሰጠው ሳይሆን፤ የክልሎቻችንን አቅም በመገንባት በራሳቸው የአስፓልት መንገድ መገንባት የሚችሉበት የአሰራር ስርዓት ወደተግባር እንዲመጣ የሚያስችለንን ጥናት አጠናቅቀን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የመሸጋገር ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡

ይህ ማለት ደግሞ የፌዴራል መንግስት ዋና ትኩረት አገርን ከአገር፣ ክልሎችን ከክልሎች የሚያገናኝና የፈጣን(ኤክስፕረስ) መንገድ የሚባሉትን በጥራትና በፍጥነት መገንባት ይሆናል፡፡ ክልሎች ደግሞ በውስጣቸው ያለውን የመንገድ ፍላጎት ለማሟላት ይሰራሉ፡፡

በዚህም መሰረት በቀጣይ አስር ዓመት የመንገድ እቅዳችን የአስፓልት መንገድ ግንባታን ጨምሮ የክልሎችን አቅም ገንብተን ራሳቸው የሚገነቡበትን አካሄድ እንጀምራለን፡፡ በዚህ መልኩ ነው እንደ ብልጽግና ፓርቲ የህዝባችንን የመንገድ ፍላጎት በቅርበት ባለው የክልል አስተዳደር ቅደም ተከተል እየተሰጠውና ምላሽ እያገኘ እንዲሄድ የምናደርገው፡፡

በተመሳሳይ የባቡር መንገድ ግንባታችንን በተለይ የአገራችንን ወጪና ገቢ ንግድ ታሳቢ በማድረግ፤በዘመናዊ መንገድ ይገነባሉ፡፡ በፓርቲያችን መሪነት የሚገነባው የባቡር ትራንሰፖርት ለአገራችን ወሳኝ የሆኑ የኮንቴይነር፣ የማዳበሪያና ሌሎችም ከፍተኛ መጠን ጭነት እና ፋይዳ ያላቸውን ግብዓቶች ወደ አገር ቤት ለማምጣት የምንችልበት ይሆናል፡፡ በአገር ውስጥ የተመረቱ ምርቶችንም ባጠረ ጊዜ ወደ ውጪ ልከን ተወዳዳሪ መሆን እንድንችል የባቡር ዘርፋችንንም አሁን ያለበትን አፈጻጸም ይበልጥ ለማሳደግ ተጨማሪ የባቡር ሃዲዶችን ለመገንባት፤ በተለይም ውጤታማነትን ለመጨመር የሚያስችል የግሉ ዘርፍንም የሚጋብዝና የሚያሳትፍ የአሰራር ስርዓት ቀርጸን ተግባራዊ አድርገናል፡፡

በመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍም በተለይ የአገልግሎት አሰጣጡን እና በከተሞች ያለውን የህዝብ ትራንስፖርት ችግር ምላሽ ለመስጠት ዘርፉን በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የግል ባለሃብት ከውጪ መጥቶ መሳተፍ የሚችልበትን እድል ፈጥረናል፡፡ ይሄም ዘመናዊ አማራጮችን ለህዝባችን ለማቅረብ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን አውቶቡሶችን (ለምሳሌ፣ በመጪው አምስት ዓመት ወደ ሁለት ሺህ አውቶቡሶች)፣ እንዲሁም ለአውቶቡስ ብቻ የተከለሉ የፍጥነት መንገዶች (ለምሳሌ፣ በአዲስ አበባ ሰባት የሚደርሱ)  እንዲኖሩ እንሰራለን፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር እንደመሆኑ ሰው የሚይስፈልገውን ነገር ለመስጠት ጥረት ያደርጋል፡፡ በዚህም መነሻ በተለይ በከተሞች አሁን እየታየ እንዳለው የእግረኛ መንገዶችን በስፋት ይገነባል፡፡ የቢስኪሌት መንገዶች ይስፋፋሉ፤ በብዙሃን ትራንስፖርት ዘርፉም በትኩረት ይሰራል፡፡ የከተማ ቀላል ባቡርም አሁን ካለበት አቅም በማሻሻል  ከፍተኛ ቁጥር ያለው የከተማ ነዋሪ ማስተናገድ እንዲችል የሚደረግ ይሆናል፡፡

የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂያችን በአገራችን ባሉ ወደ 69 የሚጠጉ ከተሞች እንዲስፋፋና እንዲተገበርም ስትራቴጂ አውጥተን እየሰራን ሲሆን፤ ስትራቴጂያችንን መተግበር የምንችልበት ምዕራፍ ላይም በመድረሳችን ከህዝባችን ጋር ሆነን ወደተግባር እናስገባለን፡፡

ከዚህ ቀደም ተጀምረው የተወሰነ ውጤት የታየባቸው፤ ነገር ግን በአፈጻጸም ጉድለት ወደኋላ የቀሩት የገጠር መንገድ ተደራሽነትን የማረጋገጫ ፕሮግራም በጥናት ላይ ተመስርቶ በአዲስ መልክ መልሰን ጉድለቱን ሊያርምና ጠቀሜታውን ማስፋት በሚያስችለን መንገድ ወደተግባር ለማስገባት ዝግጅታችንን አጠናቅቀናል፡፡

በዚህም መንገድ መስራት ብቻ ሳይሆን በተገነባው መንገድ ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት ማቅረብ ስለሚያስፈልግ፤ አሁን ላይ ያለውን የ68 በመቶ የገጠር መንገድ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚነት በአምስት ዓመት ውስጥ እስከ 90 በመቶ እንዲያድግ ፓርቲያችን አመራር ጠንክሮ ይሰራል፡፡ ይሄም አርሶአደሩ ምርቱን ወደገበያ ለማድረስና የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ያለበትን ችግር ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለን ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ከለውጡ በፊት በነበረው አሰራር መንገዶች በጀት ተይዞላቸው ይጀመራሉ፡፡ ነገር ግን በጊዜም በጥራትም እጅግ በጣም ብዙ እየጎዱን ያሉ ጉዳዮች መኖራቸውን ባከናወንናቸው ጥናቶችና ልምዶች አይተናል፡፡ እናም እንደ ብልጽግና ፓርቲ በአስር ዓመት እቅዳችን አንዱ መሰረታዊ ለውጥ የምናመጣበት መስክ ይሄ መሆኑን ግብ በማስቀመጥ እየሰራንበት ነው፡፡ በዚህም የምንገነባቸው መንገዶች በጥራት፣ በተያዘላቸው ጊዜና በጀት መጠናቀቅ አለባቸው የሚል ጽኑ አቋም ይዘን እንሰራለን፤ እየሰራንም እንገኛለን፡፡

ምክንያቱም ይሄንን ባለማድረጋችን አገራችን በቢሊዬኖች የሚቆጠር ኪሳራን ታስተናግዳለች፡፡ ይሄንን ይዞ መቀጠል አይገባም በሚል አቋምም ካሁን በኋላ የምንገነባቸው መንገዶች በተያዘላቸው በጀት፣ ጊዜ እና የጥራት ደረጃ እንዲገነቡ በማድረግ ኢትዮጵያችን በዚህ ምክንያት እያጣች ያለውን በቢሊዮን የሚቆጠር ሃብት ለማስቀረት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አድርገናል፡፡

እነዚህ ያዘጋጀናቸው የፖሊሲ ሰነዶችና ስትራቴጂዎች ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም ተሞክሮ መሆን የሚችሉበት ደረጃ ላይ ያሉና ሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማትም በዚያው ልክ እየመሰከሩለት ያለ ነው፡፡ ስለሆነም ይሄንን በእጃችን ያለውን ፖሊሲ ከህዝባችን ጋር ሆነን በመለወጥ የህዝባችንን ህይወት ወደ ሙሉ ብልጽግና ለማሸጋገር በምናደርገው ጥረት ውስጥ ህዝባችን ብልጽግናን-የሚበራውን አምፖል በመምረጥ የጀመርነውን የተስፋ ጉዞ ወደላቀ ደረጃ እንድናሸጋግር ድምጹን እንዲሰጠን ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

እኛ ብልጽግና ነን!

Loading

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *